Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ ተቋም የመገንባትና ስርዓት የመዘርጋት ስራ በትኩረት እየተሰራ ነው – ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ
የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) በተለያዩ ሁነቶች ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።
ክብርት ሚኒስትሯ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት÷ የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ”የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል። በዓለም ለ115ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረው በዓሉ ባለፉት 50 ዓመታት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚዳስስ መልኩ እንደሚከበር ተናግረዋል። አከባበሩ የሴቶችን መብቶች ወደ ተጨባጭ የኑሮ ለውጥ በመቀየር የሴቶችን የሐብት ክፍፍል፣ የማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በሴቶች ተሰርተው የመጡ ድሎችን ማስቀጠልና በሴቶች ተጠቃሚነት ላይ ያሉ ማነቆዎችን በመፈታት ቀጣይነት ያለው የኢትዮጵያን ሴቶች ብልጽግና ማረጋጋጥ ላይ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡በዚህ መሰረትም ባለፉት 50 ዓመታት ሴቶች እንዴት ተጠቃሚ ሆኑ፣ የተገኙ ተጨባጭ ለውጦችስ ምንድናቸው የሚለውንና ሌሎች ሥራዎችን የሚዳስስ ሰነድ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል። የለውጥ ዓመታት የሴቶችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል ያሉት ክብርት ሚኒስትሯ÷ ለአብነትም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ሴቶችን ወደ አመራርነት ማምጣት መቻሉን አንስተዋል።
በተጨማሪም 50 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች የካቢኔ አባላት ሆነው ቁልፍ ሴክተሮችን እንዲመሩ መደረጉን ገልፀዋል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሁን ላይ ሴቶች 41 በመቶ የሚሆነውን መቀመጫ አግኝተው የወከላቸውን ማሕበረሰብ እያገለገሉ እንደሚገኙ አብራርተዋል:: በማሕበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ጠንካራ ተቋም የመገንባትና ስርዓት የመዘርጋት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በአካባበሩ 30 ሚሊየን ሴቶች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እንዲወስዱ እንዲሁም የጡትና የማሕጸን ጫፍ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ በትኩረት እንደሚሰራ ክብርት ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
