በወጣቶች ሰላምና ደህንነት ድርጊት መርሃ ግብር (YPS) ዙርያ ምክክር መድረክ ተካሄደ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ ቁጥር 2250 (UNSCR 2250) ላይ የተመሠረተውን የወጣቶች የሰላም እና ደህነት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር ለማዘጋጀት በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ  የምክክር  እና ግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሄዷል።

‎‎የግብዓት ማሰባሰብ መድረኩ የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስተር ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህል፣ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር በወጣቶች ሰላምና ደህንነት (Youth peace and security-YPS) ዙሪያ ለክልሉ ወጣቶች፣ ወጣት አደረጃጀት እና ባለድርሻ አካላት የግብዓት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ አካሂዷል። ‎በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክትል የቢሮ ኃላፊና ወጣቶች  ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኡመር መሀመድ ዱባ ወጣቶች ለሰላም ያላቸው ሚና የጎላ ሲሆን ሰላም ለማስጠበቅ ወጣቱ ግንባር ቀደም መሆኑን በመጥቀስ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ወጣቱ በሙሉ አቅሙ ለሀገሪቱ ዘብ መቆም እንዳለበትና የወጣቱንም ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
‎
‎አክለውም ወጣቱን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዛሬ ያዘጋጀውን የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ የክልሉ ወጣቶች ገንቢ አስተያየቶችን በመስጠት እና በማዳበር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጀመረውን የወጣቶች የሳም እና ደህንነት ድርጊት መርሃ ግብር ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
‎‎ለምክክር መድረኩ መነሻ ሰነድ ያቀረቡት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የብሔራዊ  አገልግሎት ማስፋፊያ ዴስክ ኃላፊ  በበኩላቸው የግብዓት ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ወጣቶችን በሰላም ግንባታ፣ በድርድር እና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ ተሳታፊ በማድረግ፣ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ያለመ የወጣቶች የሰላም እና ደህንነት የድርጊት መርሃ ግብር በማዘጋጀት  ወጣቶች በግጭት መከላከል ስራዎች ላይ ያላቸውን ሚና ለማጉላት ያለመ ነው ብለዋል።

 

በዚህ ግብአት ማሰባሰቢያ መድረክ  የድንጋጌው(UNSCR 2250) የተቀመጡ አምስት አምዶች(pillars ) ተሳትፎ፣ መከላክል፣ ጥበቃ፣ አጋርነት፣ መነጠል እና ማዋሀድ ላይ መሰረት በማድረግ ግብአት ማሰባሰቡ የተቻለ ሲሆን። ‎በዚህ መድረክ በክልሉ ያሉ የተለያዩ ወጣት አደረጃጀቶች፣ አካል ጉዳተኛ ወጣቶች፣ ሴቶች ፣ ባለድርሻ አካላት እና በሰላም ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት ተወካዮች በውይይቱ ተሳትፈዋል።

Please follow and like us: