በሩሲያ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በተካሄደው የብሪክስ (BRICS) ወጣቶች ኮንፈረንስ ላይ ላደረጉት አስተዋጽኦ የኢፌድሪ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር) ከሩስያው ፕሬዚዳንት የላቀ የምስክር ወረቀትና የክብር ሜዳሊያ ተበረከተላቸው፡፡

የኢፌድሪ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር) በኢትዮጵያ የሩሲያ ፌዴሬሽን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ኤቭጌኒ ተሬኪንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው በማነጋገር በወጣቶች ልማትና በብሪክስ እና አህጉራዊ ተሳትፎ ዙሪያ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ አምባሳደር ኤቭጌኒ ተሬኪን በሩሲያ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በተካሄደው የብሪክስ (BRICS) ወጣቶች ፌስቲቫልና ኮንፍረንስ ላይ ክብርት ሚኒስትር ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ፣ አመራርና ውጤታማ ተሳትፎ በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተፈረመ የላቀ የምስክር ወረቀት እና የክብር ሜዳሊያ አበርክተውላቸዋል። ኤርጎጌ ተስፋዬ( ዶ/ር) ለተደረገላቸው ከፍተኛ እውቅና ምስጋናቸውን አቅርበው በኢትዮጵያና በመላው አፍሪካ የሚገኙ ወጣቶችን አቅም ለመገንባትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ከሩስያ ፌዴሬሽን ጋር በትጋት እንደሚሠሩ በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የሽልማት ሥነ ሥርዓቱን ተከትሎ ሁለቱ የሥራ ኃላፊዎች በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የወጣቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ስልታዊ መንገዶች ላይ በስፋት መክረዋል፡፡አምባሳደር ኤቭጌኒ ተሬኪን በበኩላቸው በሩሲያና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ታሪካዊና ጠንካራ ወዳጅነት በማንሳት የሁለቱን አገራት ወጣት ትውልዶች በተለያዩ የልማትና የትብብር መስኮች ላይ በስፋት ለማሳተፍና ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መንግሥታቸው በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።

Please follow and like us: