በሀገር አቀፍ ደረጃ በሴቶች የሚመሩ አደረጃጀቶችን ለማጠናከር ያለመ ፕሮጀክት በጋራ ለመተግበር የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት ተካሄደ

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ አዲስ የተሾሙትን የኬር ኢትዮጵያ ሀገራዊ ዳይሬክተር ዶ/ር ማህተመ ምክረ እና አጋራቸውን ተቀብለው በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

‎‎የስራ ሃላፊዎቹ በዋነኛነት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሴቶች የሚመሩ አደረጃጀቶችን ለማጠናከር ያለመ ፕሮጀክት በጋራ መተግበር ላይ ያተኮረ ምክክር አድርገዋል። ክብርት ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ፥ ኬር ኢትዮጵያ በቅርቡ ለፀደቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ማብቃትና የስርዓተ ፆታ እኩልነት ፖሊሲ ግብዓት የሚሆን መነሻ ጥናት በጋራ በማካሄድ እንዲሁም የተቋማት አካቶ ትግበራ የምዘና ማዕቀፍ ዝግጅትና በሌሎችም ዘርፎች ላበረከተው ጉልህ አስተዋፅዖ ምስጋና አቅርበዋል።
‎

በቀጣይም የሴቶች መብት ጥበቃ ላይ የሚሰሩ አደረጃጀቶችን አቅም ማጎልበትን ጨምሮ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሳደግ፣ የተቋማት አካቶ ትግበራ አሰራርን ማጠናከር እና በስርዓተ ፆታ እኩልነት ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በትብብር ለመስራት የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል። በተቋማቱ መካከል የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እና በሌሎች አዳዲስ የትብብር መስኮች ዙሪያ ያላቸውን አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም የስራ ሃላፊዎቹ ተስማምተዋል።

Please follow and like us: