‎ለህዝብ የተገባን ቃል ማክበር፣ አገልጋይነትን በተግባር ማሳየትና በላቀ ትጋት መስራት ይጠበቅብናል

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር “ከምርጫ ድል ማግስት፤ ለጠንካራ መንግስት!” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ከሠራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል።

‎‎ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፥ ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለማህበራዊ አካታችነት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ በርካታ ውጤታማ ተግባራት መከናወኑን፤ ሆኖም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ገልፀዋል። ‎7ኛው ሀገራዊ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የተቋሙ ሰራተኞች እንዲሁም መላው ኢትዮጵያውያን ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን እና አደረጃጀቶች ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን በመጥቀስ ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል። ‎በቀጣይም የህዝብን አደራ በማክበር፣ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረምና አገልጋይነትን በተግባር በማሳየት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። ‎ሀገራዊ ምርጫን ጨምሮ በማንኛውም ሁነት ወቅት የተቋሙ ሰራተኞች አገልግሎት አሰጣጥ ያለመቆራረጥ መቀጠልና የተጀመሩ ስራዎችንም በተቀመጠው ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

‎‎የውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የሚኒስቴሩ የማህበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሁሪያ አሊ፤ የድህረ ምርጫ ስራዎችን ተቋሙ ከተሰጡት ተልዕኮዎች ጋር በማስተሳሰር ያለማንጠባጠብ በዕቅዱ መሠረት መፈፀም ጉልህ ሀገራዊ እንድምታ እንዳለው አስገንዝበዋል። ‎በምርጫ ማሸነፍ የመጨረሻ ግብ አይደለም፤ ይልቁንም የህዝብ ፍላጎት የሚጨምርበት፣ ህዝብና መንግስት እንደ አዲስ ውል የሚገቡበት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ከፉክክር አልፈን ወደ ብሔራዊ ትብብር የምንሸጋገርበት፣ የተሰጠንን አደራም ተረክበን ተስፋውን እውን ለማድረግ በጋራና በቁርጠኛነት መስራትን የሚጠይቅ ሂደት በመሆኑ በትጋት መረባረብ እንደሚገባ ተናግረዋል። ‎እንደተቋም በድህረ ምርጫ አካታች ልማትን ለማረጋገጥ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የገባነውን ቃል በተጨባጭ ወደ መሬት የማውረድና የማሳካት ስራ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።

‎‎በሪፎርም ስራችንም ጠንካራ ተቋም በመገንባት፣ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት፣ ቀልጣፋና የተፋጠነ አገልግሎት በመስጠት የህዝብን እርካታና አመኔታ ማሳደግ ይገባል ብለዋል። ኢትዮጵያ ሰላሟ የተጠበቀ፣ እድገቷ የተፋጠነ፣ ጠንካራ የዴሞክራሲ ስርዓት የተገነባባትና የፀናች ሀገር እንድትሆን ተግባራችንን በላቀ ዲሲፕሊንና በውጤታማነት መፈፀም ይገባል ብለዋል። ‎ገለፃውን ተከትሎ በሰራተኞች የተነሱ ሀሳቦች፣ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ላይ ሰፊ ውይይት የተካሄደባቸው ሲሆን ተቋማዊ አፈፃፀሞችን በመገምገም በቀጣይ እቅድ በማካተት በትኩረት መፈምፀ የጋራ መግባባት ተደርሷል።

Please follow and like us: