Phone: +25111111111 Email: info@mowsa.gov.et
”ድጋፋችንን ለሚሹ ወገኖች ደም እንለግስ – ህሙማንን እንርዳ – ህይወት እንታደግ – ለሌሎች አለኝታና ተስፋ እንሁን!” – ክብርት ሙና አህመድ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶችን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎን ለማጎልበት የሚያስችሉ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት፣ የክረምትና የበጋ ወራት የስምሪት መርሃ – ግብሮችን በማዘጋጀት በተለያዩ የስምሪት መስኮች የወጣቶችን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን በመምራትና በማስተባበር ላይ ይገኛል።
በዚህም የተሳታፊዎች ቁጥር እንዲሁም በአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ አገልግሎቱ ለሀገር ብልፅግናም ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም የ2018 ዓ.ም የክረምትና የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሀ – ግብር በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በተጠናከረ አግባብ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል። ከተለዩ 14 የስምሪት መስኮች ውስጥ የጤና አገልግሎት አንዱ ሲሆን የደም ልገሳ አገልግሎት ደግሞ በዋነኝነት ይገኝበታል። በመሆኑም ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ጋር በመተባበር “በጎነት መገለጫችን፤ ደማችን ለወገናችን!!” በሚል መሪ ቃል ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ.ም በአንድ ጀምበር የ10 ሺህ ዩኒት የደም ዘመቻ ለማካሄድ አቅዶ በቅንጅት እየሰራ ይገኛል፡፡
ለዚህም በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች መርሀ – ግብሩን ለማሳካት የሚያስችል የንቅናቄ እና የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተካሄዱ ናቸው። ስለሆነም ድጋፋችንን ለሚሹ ዜጎች ደም እንለግስ – ህሙማንን እንርዳ – ህይወት እንታደግ – ለወገኖቻችን አለኝታና ተስፋ እንሁን!
ክብርት ሙና አህመድ
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ
