የሶማሌ ክልል የወጣቶች ምክር ቤት በይፉ ተቋቋመ

የሶማሌ ክልል የወጣቶች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በይፋ ተቋቋመ።

በምስረታ መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ሙና አህመድ ወጣቶች ካላቸው እምቅ አቅም፣ እውቀትና ክህሎት አንፃር ራሳቸውን ከመለወጥ ባለፈ ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት የወጣቶችን ችግሮች ለመፍታት፣ መብታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ህገመንግስቱንና ፖሊሲውን መሠረት በማድረግም ባለፉት አመታት በርካታ የወጣት አደረጃጀቶች ተቋቁመው የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናወኑ መቆየታቸውን አንስተዋል።

ሆኖም እንደሀገር በመንግስትና በወጣቶች መካከል ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል፣ በወጣቶች የሚመራና ከመንግስት ጋር በመመካከር የሚሰራ፣ እውነተኛ የወጣቶች ድምፅ የሚሆን ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በሱማሌ ክልል ምክር ቤቱ እንዲቋቋም መደረጉም በተለይ የክልሉን ወጣት ድምጽ ለመስማት፣ ፍትሃዊ አሰራሮችን ለመዘርጋትና ተጠቃሚነትን ለማስፈን ባጠቃላይም በወጣቶች ህይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን ለማሳካት የላቀ አስተዋጽዖ ያበረክታል ብለዋል።

ወጣቶች በተደራጀ አግባብ ለክልሉ ሁለንተናዊ እድገት የድርሻቸውን መወጣት እንዲችሉ የምክር ቤቱ መቋቋም ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ለክልሉ ወጣቶች እና አመራሮች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ምክር ቤቱ ዓላማውን እንዲያሳካ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዋ ለተመረጡ ስራ አስፈጻሚ አካላት መልካም የስራ ዘመን ተመኝተዋል፤ ኃላፊነታቸውንም በአግባቡ እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሶማሌ ክልለ መንግስት ምክትል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ኢብራሂም ኡስማን ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም፣ እውቀትና ክህሎት በአግባቡ መጠቀም ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን በጽኑ መሠረት ላይ ማነጽ ነው ብሏል።

በመሆኑም በቀጣይ የክልሉ ወጣቶች ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ ተግባራት ለማከናወንና ምክር ቤቱን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል የጠቅላላ አባላት ምርጫ የተከናወነ ሲሆን ምክር ቤቱን በቀጣይ አመታት የሚመሩ ስራ አስፈጻሚ አካላት ምርጫም በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል። በዚህም ወጣት መሀመድ አህመድ ኑር የክልሉ የወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆኖም ተመርጧል።

Please follow and like us: